ጤናማ እና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው- አቶ አዲሱ አረጋ

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በስፖርት የበለፀገ እና ተተኪ ስፖርተኞችን በክልሉ ለማፍራት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል፡፡

በአቶ አዲሱ የተመራው ልዑክ በሱሉልታ እየተገነባ የሚገኘውን የስፖርት አካዳሚ ጎብኝቷል።

አካዳሚው አንድ ቢሊዮን ብር በሚሆን ወጭ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን በውስጡም ከ13 በላይ የስፖርት ስልጠናዎች የሚሰጥበት እና ዓለም አቀፍ የፊፋ ደረጃን ያሟላ እንደሆነ ተገልጿል።

ተመሳሳይ የስፖርት አካዳሚዮች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዮች ላይ እየተገነቡ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አዲሱ ይህም የክልሉ መንግስት ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ተብለዋል።

የሱሉልታ የስፖርት አካዳሚ ሁሉንም የስፖርት አይነት መስጫ ማዕከላትን እና ለዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስፈልጉ እንደ የአሰልጠኞች መኖርያ ቤቶች፣ የስልጠና የመማርያ ክፍሎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።

የአካዳሚው ግንባታ ከተጀመረ አምስት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን ስራው 90 በመቶ የተገባደደ፣ 13 የስፖርት አይነቶችን ማሰልጠን የሚያስችልና 800 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት፣ በ20 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑ ተገልጿል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የክላስተር እና የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባው በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ቢጓተትም አሁን በተቀመጠለት የግዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ መንግስት ከፍተኛ ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ግንባታው በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉ አንጋፋ አትሌቶች እንደ የስታድየም ወንቀሮች፣ የመሮጫ አሸዋ እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንዲሟሉና በተቀመጠለት የግዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አሳስበዋል፡፡

(በሚልኪያስ አዱኛ)