በሕገ-መንግስት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

መጋቢት 6/2016 (አዲስ ዋልታ) በሕገ-መንግስት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአሰራር ሥነ-ስርዓት ረቂቅ ደንብ ላይ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ያዘጋጀው የውይይትና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሠብሳቢ ቴዎድሮስ ምህረት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአጣሪ ጉባዔው የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ 11 የጉባዔ አባላት የሚመሩት በሕገ-መንግስቱ የአሰራር ሥነ-ስርዓት መሻሻያ ላይ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው ብለዋል።

ተቋሙ ሕገ-መንግስታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የውሳኔ ሃሳቦችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አደራጅቶ በማቅረብ ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በአሁኑ ሰዓትም ከ100 በላይ የሕገ-መንግስት ትርጉም ጥያቄዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረባቸውን አስታውቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በሕገመንግስት ጉዳዮች ላይ የአቤቱታና ቅሬታ አቀራረብ መመሪያ በማዘጋጀት ስራ ላይ ለማዋል እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በረቂቅ ደረጃ ያዘጋጀው የአሰራር ሥነ-ስርዓት ደንብ ግብዓት ታክሎበት ጸድቆ ስራ ላይ ይውላል ብለዋል።

የዜጎች የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እያከናወነ ያለውን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የአሰራር ሥነ-ስርዓት ደንቡ ስራ ላይ ሲውልም ለዜጎች የፍትሕ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የራሱን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና የሕገ-መንግስት አጣሪ ጉባዔ ሠብሳቢ ቴዎድሮስ ምህረት አጣሪ ጉባዔው የሕገ-መንግስት የትርጉም ጉዳዮችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል ብለዋል።

ለተቋሙ የሚቀርቡ የሕገ-መንግስት ጉዳይ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትም የአሰራር ሥነ-ስርዓት ደንብ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ለሕገ-መንግስት ትርጉም ጉዳዮች እልባት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በአሰራር ሥነ-ስርዓት ደንብ ዝግጅት ሂደት ላይ የግብዓት ማሰባሰብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።

የሕገ-መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአሰራር ሥነ-ስርዓት ረቂቅ ደንብ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር እየተደረገበት እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል።