በመስዋዕትነት የተገኘ ድል በጫና አይቀለበስም

በነስረዲን ኑሩ

ጥቅምት 22/2015 (ዋልታ) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን አሳፋሪ ክህደት ተከትሎ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀው ጦርነት ሁለት አመታትን ሊደፍን የቀናት እድሜ ብቻ ቀርቶታል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያጵያውያን ከባድ የሚባል ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ የሚሳናቸው የለምና ዋጋ ተከፍሎበትም ቢሆን ሁሉንም እንደየአመጣጣቸው እየመከቱ ይገኛሉ፡፡

ከጦርነት የሚያተርፈው የጦር መሳሪያ ነጋዴ ብቻ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሄድ መለስ ሲል በከረመው ጦርነት ለሞት፣ እንግልት፣ መፈናቀል፣ ንብረት ውድመት፣ አስገድዶ መደፈር እና ለተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መዳረጋቸው አልቀረም፡፡

ከሰሜን እዝ ጥቃት በኋላ በ17 ቀናት የመልሶ ማጥቃት አከርካሪው የተሰበረው ትህነግ አብዛኛው አመራሮቹ ተገድለውበት እና ተማረከውበት የተበተነ ቢሆንም በስፖንሰር አድራጊዎቹ ፖለቲካዊ ድጋፍ ዳግም ማንሰራራቱ ይታወሳል፡፡

ይህ ጦርነት በውስን ምዕራባዊያን ሀገራት ስፖንሰር አድራጊነት እና በአሸባሪው ህወሓት ፈጻሚነት የሚካሄድ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከአንድ ታጣቂ የሽብር ቡድን ጋር ብቻ የምታደርገው ጦርነት እንደሆነ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

ምዕራባውያን እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አሸባሪው ቡድን ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ ኢትዮጵያን ዳግም እንዲወጋ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ሀይሎች ትህነግ እንያሸነፈ ሲመስላቸው ዝምታን፤ አለፍ ሲልም ሙገሳን ምርጫቸው በማድረግ የኢትዮጵያን መሸነፍ በተስፋ ከመጠበቅ ባለፈም አዲስ አበባ ተከበበችን ጨምሮ ለቁጥር የሚታክቱ የበሬ ወለደ ትርከቶችን በሚዲያዎቻቸው ሲያስተጋቡ መክረማቸውም አይረሳም፡፡

የማደጎ ልጃቸው ትህነግ በአፋር እና አማራ ክልሎች ወረራ በመፈጸም ለጆሮ የሚቀፉ ግፎችን በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽም፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ሲያወድም፣ የእርዳታ እህልን ጨምሮ ነዳጅና ሌሎችንም ንብረቶች ሲዘርፍ እሰይ አበጀህ በሚመስል መልኩ ጸጥ ረጭ ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡

እነዚህ አካላት ህልማችንን ያሳካልናል ብለው ተስፋ የጣሉበትን አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአንቀልባቸው አዝለው አራት ኪሎ ካላደረስነው ሞታችን ነው ብለው የጀመሩት መንገድ ብዙም ሊያስኬዳቸው አልቻለም፡፡

ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት መከራዎች ከመፍረስ ይልቅ የምትጠነክር፤ በአንድ እጇ ሉአላዊነቷን እያስከበረች በሌላኛው ልማቷን የምታሳልጥ፤ የሚገጠሟትን ፈተናዎች በጽናት እና በጀግንነት የምትሻገር፤ ፈረሰች፣ አበቃላት ያሏትን ሟርተኞች ኩም የምታደርግ የተአምር ሀገር መሆኗን በማስመስከር ላይ ናት፡፡

የሆነው ሆኖ ያ በኢትዮጵያ ላይ የነበረንን አዛዥ ናዛዥነት መልሶ ይሰጠናል በሚል የተማመኑበት ትህነግ ግን 3ኛ ዙር ጥቃትና ወረራ በመፈጸም በመንግስት ሆደ ሰፊነት አግኝቶት የነበረውን የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ ገደል የከተተው ሲሆን ዛሬ ላይ የጋላቢዎቹን ህልም ማሳካት ሳይሆን ህልውናውን መታደግ እንኳን ከማይችልበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

ይህን የተገነዘቡት አንዳንድ ምዕራባዊን እጅግ በተደራጀ፣ በተተናበበ እና አይን ባወጣ ሁኔታ ትህነግን ከሞት የማዳን ትግል ላይ ይገኛሉ፡፡

አሸባሪ ቡድኑን ከተቻለ ወደ ፖለቲካ ስልጣን መመለስ ካልሆነም ህልውናው ሳያከትም ቀጣናውን በአሸባሪነት እያመሰ እንዲቀጥል የማድረግ ትግሉ የቆየ እና የተለመደ ቢሆንም የሰሞኑ ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት ሆኗል፡፡ ዛቻና ማስፈራሪያም ታክሎበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ለሚደረገው የሰላም ንግግር ቁርጠኛ እና ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ያሳወቀ ከመሆኑም በላይ በንግግሩ ላይ ተወካዮቹን ማሳተፉም ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ የሰላም ንግግር ላይ በአደራዳሪነት ለመሳተፍ ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርገው ያልተሳካላቸው ሀገራት በታዛቢነት ስም ያገኙትን የመሳተፍ ዕድል በመጠቀም፤ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወገድ ከጫፍ የደረሰውን አሸባሪ ቡድን ለማትረፍ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵ መከላከያ ሰራዊትን በትር መቋቋም ያልቻለው ትህነግ ታሪክ ሊሆን ከጫፍ በደረሰበት በዚህ ወቅት አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ትህነግ ጊዜ እና ፋታ በማግኘት ለኢትዮጵያ ሌላ የመከራ ዘመን እንዲደግስ በመንግስት ላይ ግልጽ የሆነ ጫና እያሳደሩ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በተባበሩት መንግታት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ በቅርቡ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት ዛቻና ማስፈራሪያ አዘል መልዕክት የምዕራባዊያንን ፍላጎት በግልጽ ያመላከተ ነበር፡፡

አምባሳደሯ ፍጹም ዲፕሎማሲያዊ ባልሆነና ድፍረት በተሞላበት መንገድ በሰላም ንግግሩ ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን አልቀበልም በሚል አካል ላይ አሜሪካ እርምጃ ትወስዳለች፤ ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋለች ብለዋል፡፡

ይህም ማለት ኢትዮጵያ ሆይ እኛ ያዘጋጀነውን እና በትህነግ የሚቀርበውን የንግግር አጀንዳዎች ሳታንገራግሪ ተቀበይ ማለት ነው፡፡

ፍርሃት ራሱ የሚፈራው ይፈልጋልና በሀገራችን ሉአላዊነት ላይ የሚሰነዘር ዛቻና ማስፈራሪያ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና የአውሮፓ ህብረት የተቋቋሙበትን አላማ ወደ ጎን በመተው ለአሸባሪ ቡድኑ ያላቸውን ድጋፍ በማሳየት ላይ የተጠመዱ ሲሆን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ቃል አቀባያቸው ኔድ ፕራይስ እና የአሜሪካ ሴናተሮች በተከታታይ የሚሰነዝሯቸው ያልተገቡ ጫናዎች፣ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ላላው ጫና ማሳያዎች ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ፒኤችዲ) ከቀናት በፊት ባደረጉት ንግግር ዘንድሮ በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉትን ግፍ የተሞላባቸው ጫናዎች የተቋቋምነው በፈጣሪ ድጋፍ እና በኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት መሆኑን መግለጻቸው የጫናውን ክብደት በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡

ግፍና እጅ ጥምዘዛን አምርሮ የሚጠላው የኢትዮጵያ ህዝብም በተሰማራበት ሁሉ የምዕራባዊያን ያልተገባ ጫና፣ ዛቻና ማስፈራሪ በተገቢው መልኩ እየመከተ ይገኛል፡፡

ለአብነትም በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 17 /2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ለመዶለት በተጠራው 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ያነሱት ሀሳብ ጠላቶቻችንን ያስደነገጠ ሲሆን በተቃራኒው የኢትዮጵያዊያንን እና ወዳጆቻችንን ልብ ያሞቀ ነበር፡፡

አምባሳደሩ በተሰጣቸው ሁለት ደቂቃ “ለበጎ ከሆነ ለቁም ነገር ጉዳይ፤ ጎረቤት ወዳድ ነን እንግዳ ተቀባይ፤ ግን ሀገራችንን በክፉ የሚያስቧትን፣ ቆራጥ ነን ልጆቿ አንወድም ጥቃትን” የሚለውን ሀገርኛ ዜማ ተቀኝተው ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለዘነጉ ምዕራባዊያን ግልጽ በሆነ ቋንቋ አስታውሰዋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም የምዕራባውያን ሃላፊነት የጎደላቸው አካላት ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳቸው ሲሉ የሚነዙትን ስም ማጥፋትና መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ኢትዮጵያ ታወግዛለች! በሚል ርዕስ ስር ባወጣው መግለጫ ይህ ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ሸብረክ እንደማያደርገው አረጋግጧል፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ይህን ለመሰለው አደገኛ ስም ማጥፋት ምላሽ ሳይሰጥ ታግሦ ማለፍ የሚቻል ባለመሆኑ በከፋ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸው ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ ሀገራትና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ ለማጤን መገደዱን አስረግጦ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ያወጣውን ዘርዘር ያለ መግለጫ “ይህ ጊዜ አመጣሽ የሐሰት ክስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ጨርሶ አይቀይረውም” ሲል ቋጭቷል፡፡

እኛም አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በ77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስተላለፉትን ለታሪክ የሚቀመጥ መልዕክት በማስታወስ ጽሁፉን እናብቃ፡፡

“እየሰማን ያለነው የሰላም መልእክት ሳይሆን ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ነው።

ነገር ግን በርካታ የፖለቲካ ምስቅልቅሎችን ማለፍ እንደቻለች ኩሩ አፍሪካዊት ሀገር [የተባበሩት መንግሥታት] አባል ሀገራትን አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ።

በርካታ ችግሮቻችንን ተጋፍጠን እንዳለፍናቸው ሁሉ፣ ዛሬም የገጠሙንን ችግሮች በእርግጠኝነት እንሻገራቸዋለን።

በአንዳንድ ኃያላን ሀገሮች ዐይን ፊት ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንደሆነው [ኢትዮጵያውያን] ዐቅመቢስ መስለን እንታይ ይሆናል።

ክቡር ሊቀመንበር፤ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ።

የውስጣችን መንፈስ ጽኑ ነው። የውስጣዊ መንፈሳችን ጥንካሬ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመቆም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ለመሆን እና ተግዳሮቶቻችንን ለመፍታትም ጭምር ነው።

የ120 ሚሊዮን ሕዝባችንን ዕድል ለ200 ኤክስፐርቶች ልንተወው አንችልም።

ይህንን ብዬ፤ ሁልጊዜም ቢሆን በጎ ሀሳብ ያላቸውን ተሳታፊዎች በደስታ የምንቀበል ሲሆን ሊያወግዙን እና ለሞት አሳልፈው ሊሰጡን ቀድመው የወሰኑትን ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር ይበላቸው” እላለሁ።

ስለዚህ እንደ [ኢትዮጽያ] መንግሥት ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን። ይህንንም የምናደርገው የተወሰኑ ድርጅቶችን ወይንም ኤክስፐርቶችን ለማስደሰት ሳይሆን ለራሳችን መርህ ስንል ነው።

ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚችለው በሁሉም አካባቢዎች ለተሠሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እና ፍትህ ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እንረዳለን።

ነገር ግን ይህ በሀገሪቱ ባለቤትነት መመራት አለበት። አመሠግናለሁ ክቡር ሊቀመንበር”