በመተከል ዞን በጸጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸው 194 ትምህርት ቤቶች

ቢኒያም መንገሻ

መስከረም 19/2014 (ዋልታ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር 194 ትምህርት ቤቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቢኒያም መንገሻ ገለጹ፡፡

23ኛው ክልል አቀፍ ትምህርት ጉባኤ ዛሬ በአሶሳ የተጀመረ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶቹ የተጎዱት በ2013 በመተከል በነበረው ግጭት እንደሆነና እነዚህም የመጀመሪያ፣ መካከለኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ኃላፊው በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 56 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ 138 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል የፈራረሱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ትምህርት ቤቶቹ 69 ሺሕ ተማሪዎች የሚማሩባቸው እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ከመገንባት ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ጭምር ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፣ የሽብርተኛው ሕወሓት ቡድን በተላላኪዎቹ አማካኝነት በክልሉ ያደረሰውን ጥፋት ከማውገዝ ባለፈ ችግሩ እንዳይደገም ትምህርት ቤቶቹን መልሶ ለመገንባት የተቀናጀ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

አመራሮች፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ወላጆች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡