በመንግስት የሚሰጡ መግለጫዎች የሚያመለክቱት የትግራይ ህዝብ ሳይሆን ወንጀለኛውን ህወሓትን ብቻ እንደሆነ ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ

ወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ

ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – የፌደራል እና የክልል መንግስታት የሚሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ የሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ውቅር አንድ አካል የሆነውን የትግራይ ህዝብ ሳይሆን፣ ወንጀለኛውን ህወሓት ብቻ መሆኑን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል፡፡

የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ፣ የህወሃት ፕሮፓጋንዳ አራማጆች እና አጋሮቻቸው የፌደራል እና የክልል አመራሮች የሚናገሩትን በመጠምዘዝ ለብዙ ወራት ሲሸርቡ ከቆዩት የሐሰት ዜናዎች እና አጀንዳዎቻቸው ጋር ለማጣጣም መሞከራቸውን እንደቀጠሉ አብራርቷል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሃት አሸባሪ ድርጅት እንደሆነ ማወጁን በማገናዘብ፣ የፌደራል እና የክልል መንግስት የሚሰጧቸው መግለጫዎች ሁሉ የሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ማህበራዊ ውቅር አንድ አካል የሆነውን የትግራይ ህዝብ ሳይሆን፣ ወንጀለኛውን ህወሓትን ብቻ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡