ታኅሣሥ 12/2014(ዋልታ) ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ኤድናሞል አካባቢ በሚገኘው ሞዛይክ ሆቴል ውስጥ ሲያጥቡና ሲያባዙ የነበሩ ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ግለሰቦቹ የካሜሩን እና የአይቮሪኮስት ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፥ ህብረተሰቡ ባደረሰው ጥቆማ መሰረት የፌደራል ፖሊስ በግለሰቦቹ ላይ ብርቱ ክትትል በማድረግ በትናንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማጠብና ለማባዛት ከአንድ ሰው ጋር ተስማምተው ናሙናውን በማሳየት ላይ እያሉ በሆቴሉ ውስጥ እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ታውቋል፡፡
በወቅቱም ሁለት ጥቁር ቀለም የተቀባ ሁለት ባለ 100 እና አንድ ባለ 20 የአሜሪካ ዶላር፣ 3 ሺህ የታንዛኒያ ገንዘብ፣ አንድ ባለ 10 የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ድርሀም፣ 600 የኬኒያ ሽልንግ፣ 500 የሱዳን ፓውንድ፣ 20 ሺህ የፈረንሳይ ፍራንክ እንዲሁም ለማጭበርበሪያ የሚጠቀሙባቸው የጠቆረ ዶላር መሳይ ወረቀት፣ በተለያዩ ብልቃጦች የተዘጋጀ ፈሳሽና ዱቄት ኬሚካል መሳይ፣ ማስመሪያ እና በርካታ ካኪ ፖስታዎችን በማስረጃነት ተይዘዋል፡፡
ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።
ህብረተሰቡ መሰል የማጭበርበር የወንጀል ሰለባ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊቶች ሲያጋጥሙም በአቅራቢያው ለሚገኝ ፖሊስ ጥቆማ በመስጠት የተለመደውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረግ ጥሪ ቀርቧል፡