የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በአፋር ክልል በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ጎበኙ

ታኅሣሥ 12/2014(ዋልታ) በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የተመራው የልዑካን ቡድን በአፋር ክልል በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ጎብኝቷል።

በጉብኝታቸውም በአፋር ክልል በግብርና ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን የተመለከቱ ሲሆን በዚህም በተለይ የስንዴ ፣ የጤፍ ፣ የቲማቲም ፣ የሽንኩርት እና የማሾ ማሳዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት የአፋር ህዝብ በጦርነት ግምባር ብቻ ሳይሆን በልማቱም ጀብድ እየፈፀመ መሆኑን ተመልክተናል።

የአሸባሪው ህውሃት የሀገሪቱን የሰላምና የልማት እንቅስቃሴዎችን በማወክ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር ቢንቀሳቀስም ያገኘው ምላሽ ከምኞቱ በተቃራኒው ነው ብለዋል።

ለዚህም የአፋር ክልል ህዝብና መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በተለይም በግብርናው ዘርፍ አበረታች ተግባራት እያከናወነ ስለመሆኑን አመላክተዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት መሰል ተግባራትን ማከናወን የላቀ የአመራር ቁርጠኝነት ይጠይቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በመሆኑም የክልሉ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተው እያከናወኑት ለሚገኘው አበረታች ተግባር አድንቀዋል።

አያይዘውም ሀገራችን ሁሌም እርዳታ ጠባቂ እንድትሆን ማድረግ የውጭ ሀይሎች ዋነኛ ፍላጎት መሆኑን ጠቁመው መሰል ስራዎችን ማከናወን ግን ሀገራችንን ከጥገኝነት ከማላቀቅና በምግብ ራስን ከመቻል አንፃር ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የሀረሪ ክልልም ከአፋር ክልል ጋር ያለውን ትስስርና ቅንጅትን በማጠናከር በተለይም በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

በጉብኝቱም ከሀረሪ ክልል የልኡካን ቡድን በተጨማሪ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ  እና የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሚውኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።