መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ በዘንድሮው መጋቢት ወር ብቻ ከ4 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ መከሰቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስተወቀ።
በተደጋጋሚ በፓርኮቹ ላይ የሚደርሰውን የእሳት አደጋ በዘላቂነት ለመፍታትም በሁሉም ብሔራዊ ፓርኮች ላይ “የእሳት መከላከል ብርጌድ” ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው መጋቢት ወር ብቻ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ደቡብ ክልሎች ከአራት በላይ የሚሆኑ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል።
አላይ ዴጌ አሰቦት እጩ ብሔራዊ ፓርክ፣ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወፍ ዋሻ ላይ ተመሳሳይ አደጋዎች መከሰታቸውን ገልጸዋል።
በየአመቱ እየተከሰቱ ያሉ የሰደድ እሳት አደጋዎች በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።
ከሰሞኑ በፓርኮቹ ላይ የደረሰው አደጋም እድሜ ጠገብ የሆኑ ደኖች እንዲወድሙ እና እንስሳቱም እንዲሞቱ ማድረጉን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
በአብዛኛው በፓርኮች ላይ የሚደርሱ የሰደድ እሳት አደጋዎች ሰው ሰራሽ ሲሆኑ ከህገ-ወጥ ሰፈራ፣ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ፣ አደንና ከሰል ማክሰል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ መሆናቸው ተገልጿል።