ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) በምሥራቅ ጉጂ ዞን የሚንቀሳቀሱ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ከቡድኑ አፈንግጠው በመውጣት ለጸጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን የአይን እማኞች ገለፁ።
መንግሥት የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ እያደረገ ያለውን ጥረት ተከትሎ በርካታ የቡድኑ አባላት ለጸጥታ አካላት እጃቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።
ለአብነትም ሰሞኑን ብቻ በርካታ የሽብርተኛው ሸኔ አባላት እጃቸውን ለመንግሥት የጸጥታ አካላት ሰጥተዋል፡፡
ለጉዳይ ቅርበት ያላቸው የዐይን እማኞች በምስራቅ ጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ አካባቢ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉት የቡድኑ ታጣቂዎች መካከል መሀመድ ሁሴን (ፈልማታ)፣ ጣይር አብዱሮ (ድዳ) እና ቱሳ አቡ (ለሚ) ለመንግስት እጃቸውን ሰጥተዋል።
የቡድኑን አባላት ፎቶዎች አያይዘው ለኤፍቢሲ በላኩት መረጃ ላይ እንዳመለከቱት፥ ሶስቱን የቡድኑን ታጣቂዎች ጨምሮ በርካታ አባላት በሰላማዊ መንገድ በነገሌ ቦረና ለሚገኙ የኦሮሚያ ፖሊስና ሚሊሻ እጅ ሰተጥተዋል፡፡