ከተማ አስተዳደሩ በአሸባሪው ቡድን የወደሙ ተቋማትን በማቋቋም ሂደት ተሳትፎ ማድረጉን እንደሚቀጥል ገለጸ

ታኅሣሥ 14/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሽብር  ቡድኑ ያወደማቸውን የጤና እና የትምህርት ተቋማት በማቋቋም ሂደት የነቃ  ተሳትፎ ማድረጉን እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት የሕወሓት  የሽብር ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ያደረሰውን ውድመትና ዘረፋ በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በጤና ኬላዎችና ሆስፒታሎች ላይ ያለ ርህራሄ አርፏል።

ቡድኑ ማውደም የሚችለውን አዉድሟል ፤ ነቅሎ መውሰድ የሚችለውን ወስዷል  ያሉት ከንቲባዋ በወራሪው ቡድን የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው ነፍሰጡር እናቶች፣ አረጋውያንና ህፃናት በተለይም ተከታታይ ህክምና የሚያሻቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፋ የጤና ችግር ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።

የጤና ጉዳት ለማንም ጊዜ ስለማይሰጥ  አዲስ  አበባ ከተማ  አስተዳደር የኅልውና ዘመቻው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዘርፉ በርካታ ተግባራትን እየተከናወኑ  መሆኑን ከንቲባ አዳነች  አመልከተዋል።

የወደሙ ጤና ተቋማትን በሰው ኃይል እስኪደራጁ 400 የጤና ባለሙያዎቹን ወደ ተለያዩ ግምባሮች ከመላኩም ባሻገር፣ በአጠቃላይ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ የተለያዩ መድኃኒቶች፤ የጤና መሳሪያዎችን ካለዉ ላይ ማካፈሉን ገልጸዋል።

በአማራና በአፋር ክልሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት በተለይም በ6 ሆስፒታሎች

1.የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሞላሌ ሆስፒታልን ፤

2.የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የከሚሴ ሆስፒታልን ፤

3.የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የደጎሎ ሆስፒታልን ፤

4.የራስ ደስታ ሆስፒታል የደብረሲና ሆስፒታልን ፤

5.የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የመሀል ሜዳ ሆስፒታልን ፤

6.የካቲት 12 ሆስፒታል የወረሂሉ ሆስፒታልን፤ በሰዉ ሀይል እንዲሁም በህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒት አቅርቦት ዳግም እንዲደራጁና ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ  11 ጤና ጣቢያዎችንም በማቋቋም በማጠናቀቅ ላይ  እደሚገኝ ተመልክቷል።

አሁንም ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ከከተማችን የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾችና ባለሀብቶች ጋር በመሆን በትምህር ቤት እና መሰል ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ በማደራጀት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ግብረ ሀይል ተቋቋሞ በመስራት  ላይ እንደሚገኝ  አስረድተዋል።

“ጋን በጠጠር” እንዲሉ ተቋማቱ ወደ ቀድሞ ስራቸዉ ሙሉ በሙሉ እስኪመለሱ ድረስ የምንችለውን ለማድረግ ጊዜ አንሰጥም” ብለዋል፡፡