መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – በትላንትና እለት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት የፈጸሙ የተወሰኑ ኃይሎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በዞኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል፡፡
የክልሉ መንግስት ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ በተደረገው አፋጣኝ ክትትልና እስከ አሁን በተወሰደው እርምጃ ጥቃቱን የፈጸሙ አካላት ላይ ጥቃት በመፈጸም የተወሰኑት ላይ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጿል፡፡
ይህ የጥፋት ኃይል አፍራሽ ድርጊቶችን የሚመኘው የአገር ግንባታ ተቃራኒ በመቆሙ ስለሆነ፣ የጥፋት ኃይሉ እቅድ በህዝቡ የተባበረ ክንድ እንደሚከሽፍ እንደማይጠራጠር የክልሉ መንግስት ገልጿል፡፡
የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡ በአንድነት በመቆም የዚህ የመካን ኃይል የጥፋት እቅድ እንዲያከሽፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የክልሉ መንግስት በመግለጫው፣ አገሪቱና ክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የለውጥ ምዕራፍ ሽግግርን ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጾ፣ የአገራዊ ለውጥ ተቃራኒ በመቆም የጥፋት ተግባር እየፈጸሙ ካሉ አካላት ውስጥ የጽንፈኛ ሕወሃት ቡድን ተላላኪ የሆነው ኦነግ ሸኔ መሆኑን አስታውቋል፡፡
መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በወሰደው የሕግ የበላይነት የማስከበር ስራ የኦነግ ሸኔ ኃይል እየተዳከመ የሄደ ቢሆንም፣ ይህ ኃይል ተስፋ በመቁረጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው፡፡
የጁንታ ተልዕኮ ተቀብሎ የሚንቀሳቀስ ይህ ቡድን በገጠርና በከተሞች በአመራሮችና በዜጎች ላይ ግድያ የሚፈጽሙ አካላትን በማሰማራት በርካታ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን የክልሉ መንግስት ገልጿል፡፡
በልጆቿ ደም የተገነባችሁ ኢትዮጵያ በመካን ኃይል የሽብር ተግባር አትፈርስም ብሏል የክልሉ መንግስት በመግለጫው፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በንጹሃን ዜጎች ላይ ለደረሰው ጥቃት የተሰመውን ሀዘን ገልጾ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
(በአሳየናቸው ክፍሌ)