በምግብ ራሳችንን የምንችልበት ጊዜ ቅርብ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጥቅምት 03/2013 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “በምግብ ራሳችንን የምንችልበት ጊዜ ቅርብ ነው” ሲሉ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህን የገለጹት በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል፣ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሥራ ኃላፊዎች በአርሲ ዞን ሔጦሳ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳን ከጎበኙ በኋላ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉብኝቱ ከዚህ ቀደም ለእርሻ ያልዋሉ አካባቢዎችን በማልማት ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን መመልከታቸውን በማህበራዊ ትሥሥር ገጻቸው አስፍረዋል።

በአርሲ ዞን ብቻ በምርት ዘመኑ ከታረሰው 680 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ 388 ሺሕ ሔክታር ያህሉ በኩታ ገጠም የለማ እንደሆነ ጠቅሰው ይህ ለዘርፉ ትልቅ ጅማሮ ነው ብለዋል።

የግብርና ምርታማነትን በማሻሻል በምግብ ራሳችንን የምንችልበት ጊዜ ቅርብ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ በዚህ ውጤታማ ሥራ ውስጥ ከክትትል እና ድጋፍ አንስቶ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።