የካቲት 5/2013 (ዋልታ) – በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ እንደገለጹት፣ ከኬንያ በመነሳት በምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው።
ከኬንያ ለመራባት ዝግጁ ያልሆነና በቀን በአማካይ ሁለት መንጋ አንበጣ ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ በላይነህ ገለጻ በአሁኑ ወቅት የአንበጣ መንጋው ከኦሮሚያ ክልል በአርሲ፣ በምዕራብ አርሲ፣ በጉጂ፣ በምዕራብ ጉጂና በቦረና ዞን፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ እንዲሁም በደቡብ ሶማሌ ክልል ተከስቷል።
አንበጣ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከፌዴራል መንግስት የተላኩ ባለሙያዎች ከክልሎቹ ጋር የመከላከል ስራ እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያስከትል በአውሮፕላን ከሚደረገው የኬሚካል ርጭት በተጨማሪ በባህላዊ መንገድ የመከላከል ሥራዎች አንበጣው በተከሰተበት አካባቢው ባለው ኅብረተሰብ ጭምር እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“ባለፈው ዓመት ለአንበጣ መከላከል ሥራ በሰው ኃይልም ሆነ በኬሚካል ያዳበርነው ልምድና ዝግጅት አሁን አንበጣ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ያስችለናል” ነው ያሉት።
በቀጣይ እንደ አንበጣ ያሉ ፀረ-ሰብሎችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሦስት ማዕከላት በኮምልቻ፣ በድሬዳዋና በአርባ ምንጭ ለመክፈት መታቀዱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ሰፊ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ በሰብልና በእንስሳት ግጦሽ ላይ ጉዳት ማስከተሉን ያስታወሱት አቶ በላይነህ፣ የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ጥናት እየተካሄደ መሆኑንና ጥናቱ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረት ጉዳት ለደሰረባቸው አካባቢዎች ድጋፍ እንደሚደረግም አክለዋል።
ከሚኒስቴሩ በተጨማሪ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት /ፋኦ/ ለኬሚካል ርጭት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች፣ የተሽከርካሪ፣ የገንዘብና የባለሙያ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።