በሩስያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የአሜረካን የዶላር የበላይነት ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቆመ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) በሩስያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የአሜረካን የዶላር የበላይነት ሊቀንስ እንደሚችል ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ገለጸ፡፡
የዓለምን ዓይንና ጆሮ ከሳበ 36ኛ ቀኑን ያስቆጠረው የሩስያና ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
ከዩክሬን ጎን የተሰለፉት ምዕራባዊያንና አሜሪካ በሩስያ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀቦችን ቢጥሉም ነገሩ በቀላሉ የሚቋጭ አልሆነም፡፡ ይልቁንም በሩስያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የአሜረካን የዶላር የበላይነት ሊቀንስ ይችላል ሲል ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ገልጿል፡፡
አይ ኤም ኤፍ በሩስያ ላይ የተጣለው የፋይናንሼያል ማዕቀብ የአሜሪካን የዶላር የበላይነት ሊቀንሰው ይችላል ያለ ሲሆን በሌላ በኩል በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተበታተነ የገንዘብ ሥርዓት ሊያስከትል ይችላል ሲል ስጋቱንም አክሏል፡፡
ሩስያ በበኩሏ ከሩስያ ነዳጅም ይሁን ሌሎች ምርቶችን የሚገዙ አገራት መገበያያቸው ሩብል ብቻ እንደሚሆን ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡
ሩስያ ለዓለም ገበያ ከነዳጅ አንስቶ በርካታ ምርቶችን እንደምታቀርብ የሚታወቅ ሲሆን በሩብል ብቻ ነው የምሸጠው ማለቷ የዓለምን የግብይት ሥርዓት ወዴት ይወስደዋል የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዓለም ዐቀፉ የገንብ ተቋምም ይህ ስጋት አድሮበታል፡፡
የተቋሙ ተቀዳሚ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ጊታ ጎፒናት ከፋይናሺያል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዶላር በዚህ ምድር ዓለም ዐቀፍ መገበያያነቱ ይቀጥላል ነገር ግን ትንንሽ መከፋፈሎች የሚያደርሱት ተጽዕኖ ስለመኖሩ አክለዋል፡፡
ጦርነቱ ዲጂታል ፋይናንሱ ላይ ከክሪፕቶ ምንዛሬዎች እስከ የተረጋጋ ሳንቲምና ማዕከላዊ ባንኮች ድረስ ለውጥ መፍጠር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከሩስያ ጎን የተሰለፉ አገራት ደግሞ ከሩስያ ጋር የሚገበያዩበትን መንገድ እየወጠኑ ይገኛሉ፡፡
የሩስያና ዩክሬን ጦርነት የዓለምን ምጣኔ ሀብታዊ ፍሰት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ከምርት አቅርቦት እጥረት እስከ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ለውጥ አምጥቷል፡፡
እስካሁን በሁለቱ አገራት ጦርነት ከ4 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ከመኖርያ ቄያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ሩስያና ዩክሬን እስካሁን ከሦስት ጊዜ በላይ ለሰላም ድርድር ቢቀመጡም ነገሩ እልባት አላገኘም፡፡ አገራቱ አሁንም ለተጨማሪ ድርድር የፊታችን አርብ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
በመስከረም ቸርነት