በርግጠኝነት ጁንታው መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ


ሐምሌ 11/2013 (ዋልታ) –
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በርግጠኝነት ጁንታው መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል ሲሉ ገለጹ፡፡
የገጠምነው ጠላት የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነ ጠላት ነው። ጁንታው ያገኘውን የፖለቲካ ሥልጣን የገዛ ሀገሩን ለማፍረስ የተጠቀመ ምናልባትም በታሪክ ብቸኛው ቡድን ነው ብለዋል።
አብሮ የኖረ ሰይጣን በቶሎ አይነቀልም እንደሚባለው በግራ በቀኝ መፍጨርጨሩ አይቀርም ሲሉ አክለዋል።
“በርግጠኝነት ጁንታው መልሶ እንዳይበቅል ሆኖ ይነቀላል።
ይህ የሚሆነው ሁላችንም እንቦጩን ለመንቀል ከተረባረብን ነው። በሂደቱ ውስጥ እዚህና እዚያ ግለሰቦች ሊሳሳቱ ይችላሉ። ሐሳብ የሚከፋፍሉ መረጃዎች ሊሰሙ ይችላሉ። በግብ አንድ ሆነን የአካሄድ ክርክር ይፈጠር ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ ከግባችን አያናጥበንም። የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን የጁንታውን ዕቅድ ለመቀልበስ ተነሥተዋል። ይህ በራሱ ድል ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ጠላታቸው ማን እንደሆነ ለይተውታል። እርሱንም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ዐውቀዋል። ያንንም ያደርጉታል” ብለዋል።
ይህ አንድነታችን ያስፈራቸው ኃይሎች የሚከፋፍል የመሰላቸውን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ። ዓይነ መዓታችንን ከእነርሱ ላይ አንሥተን በገዛ ወገኖቻችን ላይ እንድንተክል ያሤራሉ። ፈጽሞ አናደርገውም ሲሉ አክለዋል።
“አሁን የፈጠርነው አንድነት የጁንታውን የጥንት ሤራ ያፈረሰ፤ ቀጥሎም የሤራውን ባለቤት የሚያፈርስ፤ በመጨረሻም የተሤረባትን ሀገር በአንድነት የሚያድስ ነው።
መከላከያ ኃይላችንና የክልል ኃይሎቻችን ተገቢውን ቦታ እየያዙ ነው። ያንን ለማወክ ትንኮሳ ይኖራል። ለዚያ ለራሳችን ቃል የገባነውን የተኩስ አቁም እያከበርን ተገቢውን ምላሽ ይሰጠዋል” ብለዋል።
ምንን፣ ለምን፣ እንዴት፣ የትና መቼ ማድረግ እንዳለብን ጥብቅ ዕቅድ አለን። ውጤቱን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወዳጅም ጠላትም ያየዋል። ሠራዊታችን አስፈላጊ ሲሆን እጅን በአፍ ላይ ለሚያስጭን ተልዕኮ ተዘጋጅቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አረሙ እንዲነቀል አድርገን እንሠራለን። አረሙን ስንነቅል ግን ስንዴውን እንዳንጎዳው የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን ብለዋል።
በሀገራችን አረም በደቦ ነው የሚነቀለው። የኢትዮጵያ ልጆችም እርሱን እያደረጉት ነው ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።