በሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ሚናዋን እንድትጫወት ሱዳን ጠየቀች


ሚያዝያ 30/2016 (አዲስ ዋልታ) በሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ሚናዋን እንድትጫወት ሱዳን ጠየቀች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሱዳን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሁሴን አዋድ አሊ መሃመድን አነጋግረዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር መሀመድ ሁሴን ኢትዮጵያ በሱዳን ሁለንተናዊ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ እየተጫወተችው ያለውን ሚና በማድነቅ በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና ወንድማማቻዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ወሳኝ ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሱዳንን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ እስካሁን የተጫወተችውን ሚና አውስተው አበርክቶዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት በሱዳናዊያን ባለቤትነትና መሪነት መከናወን አለበት የሚል ፅኑ እምነት እንዳላትም ገልጸዋል።

አምባሳደር ሁሴን በቅርቡ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ ሲሆን ኢትዮጵያን የመጀመሪያ የጉብኝታቸው መዳረሻ ማድረጋቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።