ሚያዝያ 8/2015 (ዋልታ) በሱዳን የተከሰተው ግጭት በፍጥነት እንዲቆም እና ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመጡ የአፍሪካ ህብረት አሳስቧል፡፡
ህብረቱ በሱዳን የተፈጠረውን ግጭት አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ ሁሉም የፖለቲካ አካላት፣ የመከላከያ ኃይሎች እና የፈጥኖ ደራሽ ጦር ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች ተቆጥበው የተከሰተውን ግጭት በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረበው ህብረቱ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ሁሉም አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው ቸግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ አሳስቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በበኩሉ በሱዳን ጦር ኃይሎች እና የፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) መካከል የተፈጠረው ወታደራዊ ግጭት በእጅጉ እንዳሳሰበውና በጠፋው የሰው ህይወትም ማዘኑን ገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና በአገሪቱ መረጋጋት እንዲያሰፍኑ የጠየቀው ምክር ቤቱ በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት ሁሉም የድርጊቱ ተዋንያኖች ወደ ውይይት እንዲመለሱ አሳስቧል።
ሱዳንን በጋራ በሚመሩት የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) መካከል ከቀናት መፋጠጥ በኋላ ትላንት የተጀመረው ግጭት ዜጎችን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መክተቱ ተገልጿል።
በአገሪቱ ዋና ከተማ ካርቱም በተከሰተው ግጭት እስካሁን ከ50 በላይ የታጠቁ እና ሰላማዊ ዜጎች ጭምር ህይወታቸው ማለፉን እና ከ500 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡