በቦስተን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል

ቦስተን ማራቶን

ሚያዝያ 8/2015 (ዋልታ) ነገ በሚካሄደው 127ኛው የቦስተን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል።

በአንጋፋው የቦስተን ማራቶን በሴቶች አትሌት ጎይትቶም ገብረስላሴ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል ትገኛለች።

አትሌት ጎይትቶም በሐምሌ 2014 ዓ.ም በአሜሪካ ኦሬጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ አንደኛ የወጣችበት ጊዜ በርቀቱ ምርጥ የግል ምርጥ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል።

እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው የቦስተን ማራቶን በሴቶች ያሸነፈችው አትሌት አፀደ ባይሳ ውድድሩን የማሸነፍ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ውስጥ ተካታለች።

አትሌት አፀደ እ.አ.አ በ2012 የቺካጎ ማራቶንን ስታሸንፍ የገባችበት 2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ3 ሴኮንድ የርቀቱ ምርጥ ሰዓቷ ነው።

አትሌት አባብል የሻነህ፣ አትሌት ሕይወት ገብረማርያምና አትሌት አማን በሪሶ ሌሎች በሴቶች ውድድር የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

ኬንያውያኑ አትሌቶች ጆስሊን ጆፕኮስጌይ፣ሰሌስቲን ቼፕቺርቺርና ሄለን ኦቢሪ በውድድሩ የሚጠበቁ አትሌቶች መሆናቸውንም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

በወንዶች የሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊ አትሌት ሌሊሳ ደሲሳ (እ.ኤ.አ 2013 እና 2015) የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ካገኙት አትሌቶች መካከል ይጠቀሳል።

አትሌት ሌሊሳ እ.ኤ.አ ጥር 2015 በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተካሄደ የማራቶን ውድድር 2 ሰዓት ከ4 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።

አትሌት ሹራ ቂጣታ፣ አትሌት ሄርጳሳ ነጋሳ፣ አትሌት አንዳምላክ በልሁና አትሌት አንዷለም በላይ ሌሎች በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

የወንዶች ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ኢሉይድ ኪፕቾጌ (2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ1 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ) ውድድሩን የማሸነፍ ዋንኛ ግምት አግኝቷል።

ነገ በሚካሄደው የቦስተን ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች የ150 ሺሕ ዶላር ሽልማት እንደሚበረከትላቸው የቦስተን አትሌቲክስ ማህበር አስታውቋል።

በአጠቃላይ ለውድድሩ ተሳታፊዎች 879 ሺሕ 500 ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱም ተገልጿል።