በሸካ ዞን በማሻ ወረዳ ኬዎ ቀበሌ በቡና ልማት የተሰማሩ ድርጅቶች ወጤታማ መሆናቸው ተገለጸ።

ጥቅምት 21/2014 (ዋልታ) በሸካ ዞን በማሻ ወረዳ ኬዎ ቀበሌ በቡና ልማት የተሰማሩ ድርጅቶች ወጤታማ መሆናቸው ተገለጸ።
ልኡል ቀለም ቡና እና ቅመማ ቅመም አምራች ድርጅት ከመንግስት 428 ሄክታር መሬት በመረከብ ወደስራ የተሰማራ ድርጅት ሲሆን 320 ሄክታር መሬት በቡና ተክል በማልማት ውጤታማ መሆን መቻሉ ተገልጿል።
ድርጅት 284 ቋሚ እና ጊዜያዊ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በቀን እስከ 100 ኩንታል የታጠበ ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ ያዘጋጃል።
ድርጅቱ በሚያመርተው ቡና የጥራት ተሸላሚ ሲሆን ከሀገር ውስጥ ገበያ በተጨማሪ ለውጭ ገበያም አቅርቦት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ጠቅሰዋል።
ሌላው በስራው ውጤታማ ነው የተባለለት ሞፕላክ ትሬዲንግ በ150 ሄክታር መሬት ላይ ቡና በማልማት በጸሀይ ብቻ የደረቀ ልዩ ቡና በማዘጋጀት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ለ26 ቋሚ እና 400 ጊዜያዊ ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠረው ድርጅቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ እና አርሶአደሮች ህይወት መቀየር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
የወረዳው የቡና ሻይ እና ቅመማቅመም ቁጥጥር ቡድን መሪ ካይሮ ከስቶ በበኩላቸው እነዚህ ድርጅቶች ይበልጥ ውጤታማ እና አትራፊ እንዲሆኑ ምርጥ ዘር ከመምረጥ ጀምሮ ለሰራተኞቹ ስልጠናን እስከመስጠት ድረስ በሚያስፈልገው ሁሉ እገዛ እየተደረገላቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ድርጅቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ በበጎ ፈቃድ ትምህርት ቤት እና መንገድ በማስገንባት ለአርሶ አደሮች ደግሞ ምርጥ ዘር በማቅረብ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ተገልጿል።
በሔለን ታደሰ (ከሸካ ዞን ማሻ ወረዳ)