በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በኦሮሚያ ክልል ሀዊ ጉዲና ወረዳ ዳሮ ቢሊቃ ቀበሌ በ13 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ኢፈ ቢሊቃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል፡፡

ትምህርት ቤቱ በሁለት ፈረቃ 1ሺህ 800 ተማሪዎችን የማስተማር አቅም ያለው ሲሆን፣ በውስጡ የቤተ ሙከራ፣ መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተመፃህፍትና የኮምፒውተር ላብራቶሪ ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የተሰሩትን ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ ተማሪዎችም ሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው እንዲሁም ለተሰራበት ለትምህርት አላማ ብቻ እንዲውል አሳስቧል፡፡

በሀዊ ጉዲና ወረዳ ዳሮ ቢሊቃና አካባቢው ነዋሪዎች አዲስ ወደ ተሰራው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን በመላክ እንዲያስተምሩም ጥሪ መቅረቡን ከቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በትምህርት ቤቱ ምረቃ ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡