በበጀት ዓመቱ ከ72 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰብዓዊ ድጋፍ ትግራይ ክልል ተልኳል

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ከ72 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ከአጋር አካላትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ሳይስተጓጎል እንዲላክ እያደረገ ነው፡፡
በዚህም በዋናነት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች፣ ነዳጅና መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ወደ ትግራይ ክልል መጓጓዙን ጠቁመዋል።
ከ2014 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሀምሌ ወር እስከ ግንቦት ወር መጀመሪያ ባሉ ጊዜያት ከ72 ሺህ 485 ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል መላኩንም ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ ውስጥ 61 ሺሕ 442 ሜትሪክ ቶን በላይ የምግብና የአልሚ ምግብ ድጋፍ በአፋር በኩል መጓጓዙን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከ11 ሺሕ 043 ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ደግሞ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፣ አልባሳትና ሌሎች ድጋፎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ድጋፉም በተጠቀሱት ወራት በአጠቃላይ በ223 የአየር በረራ እና በ1 ሺሕ 947 የጭነት ተሽከርካሪዎች የተጓጓዘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ 93 በሰብዓዊ ድጋፍ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች መሳተፋቸውንም ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡