ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – በሱዳን በኩል በመግባት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሽብር ለመፍጠር እና በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ170 በላይ የጸረ ሰላም ኃይሎች መደምሰሳቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
የጸረ ሰላም ኃይሎቹ በሱዳን በኩል ሾልከው በመግባት በክልሉ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አልመሃል አካባቢ ሽብር ለመፍጠር እና በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ በተወሰደ የተቀናጀ እርምጃ ነው የተደመሰሱት።
የቢሮው ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ በሰጡት መግለጫ፥ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ከክልሉ እና ከክልሉ ወጪ ከሚንቀሳቀሱ ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመፍጠር ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፥ በእነዚህ ጸረ-ሠላም ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ አካላት እንዲሁም በክልሉ ከሚገኙት የደቡብ፣ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላት ጋር በመቀናጀት እስከትናንት በተወሰደው የህግ የማስከበር እርምጃ ከ170 በላይ የሚሆኑ የጸረ ሰላም ኃይሎች ተደምስሰዋል ብለዋል፡፡
የተደመሰሱት ጸረ-ሠላም ኃይሎች በሱዳን ድንበር በኩል በመግባት በመተከል ዞን የሕዳሴ ግድብ መገኛ በሆነው ጉባ ወረዳ አልመሃል ቀበሌን እንደ ማዕከል ተጠቅመው ወደ ግድቡ የሚደረገውን የእንቅስቃሴ መስመር በመቁረጥ ሥራውን ለማስተጓጎል አላማ የነበራቸው መሆናቸውን ጭምር አቶ አብዮት ገልጸዋል፡፡
ጸረ-ሠላም ኃይሎቹ የህዳሴ ግድብ ሥራውን ከማስተጓጎል ባለፈም በክልሉ ሽብር በመፍጠር በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት የማድረስ ዓላማ እንደነበራቸውም እና አልማሃልን ማዕከል በማድረግ ወደ አማራ ክልል ለመንቀሳቀስ ዝግጅት እንደነበራቸውም የቢሮው ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ አስረድተዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም በተወሰደው እርምጃ ከተደመሰሱት ጸረ-ሠላም ኃይሎች መካከል ከ16 በላይ የሚሆኑት የአሸባሪው የሕወሃት አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተወሰደው የተቀናጀ እርምጃም ወደአካባቢው በገባው የጠላት ኃይል ላይ ከባድ ኪሳራ ማድረስ ተችሏል ያሉት አቶ አብዮት፥ ከተደመሰሱት በተጨማሪ አብረው የገቡ በርካታ የአሸባሪው የሕወሃት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች መቁሰላቸውንና መማረካቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በቀጣይም በሁሉም አካባቢዎች በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ የጀመረውን የማያዳግም እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ኃላፊው፥ የክልሉ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች በተደራጀ መልኩ በማንኛውም ቦታ በጸረ-ሠላም ኃይሉ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሆን እንዲደግፉም ጥሪ ማቅረባቸውን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።