በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መግለጫ ሰጠ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – በተመድ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በሚመለከት ያወጣውን የፕሬስ መግለጫ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ የተወሰደው ህግን የማስከበር ርምጃ የውስጥ ጉዳይ መሆኑንና ይህም የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን ጨምሮ በሀገሪቱ ህግጋቶች የሚመራ እንደሆነ የቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤቱ አረጋግጧል፡፡

በመሆኑም በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግና ሥርአትን የማስከበር ተግባር የሀገር ሉአላዊነትን በሚያስከብር ህጋዊ ማዕቀፍ መሰረት የተከናወነ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝና በቀጣይነትም ከፍ ያለ ሀብት በማሰባሰብ ድጋፍን እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል፡፡ አያይዘውም ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤቱ ወዳጅ ለሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ሁሉ ለተጫወቱት ገንቢ ሚና፣ ለሰጡት ድጋፍና ለነበራቸው ግንዛቤ ያለውን አድናቆት ገልጿል።

በሰብአዊ መብት ጥሰትና በፆታዊ ጥቃት በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መንግስት የገባውን ቃል ኪዳን በማጠናከር እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም አለም አቀፍ አጋሮች በትግራይ ክልልና በሌሎች ቦታዎች ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት ለማሟላት ድጋፋቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ መቅረቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡