ሚያዝያ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) በታንዛኒያ እየጣለ በሚገኘው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 155 ሰዎች ሲሞቱ 236 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸወ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃሲም ማጃሊዋ ገልጸዋል።
በታንዛኒያ ከሚገኙት 26 ክልሎች ውስጥ በ14ቱ አደጋው የተከሰተ ሲሆን 200 ሺሕ ሰዎች የጎርፉ ተጠቂ መሆናቸውን እና 10 ሺሕ ቤቶች መውደማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው አስታውቀዋል።
የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት፣ የእርሻ ሰብሎች፣ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ የጤና ተቋማት እና የእንስሳት እርባታ ስፍራዎች በጎርፍ ተጎድተዋል ማለታቸውንም ሲጂቲኤን ዘግቧል።
አስከፊ ሁኔታዎችን ለመከላከል በጎርፍ ክፉኛ በተጎዱ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ማድረግ እና የመሳሰሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን መንግስት ወስዷል ሲሉም ተናግረዋል።
በሌላኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር በኬንያ በዚህ ሳምንት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 32 ሰዎች ሲሞቱ ከ100 ሺሕ ሰዎች በላይ ተጎጂ መሆናቸው ይታወሳል።