ቲክ ቶክ ይሸጣል?

የቻይናው የቲክ ቶክ እናት ካምፓኒ ባይትዳንስ ቲክ ቶክን ለመሸጥ ምንም እቅድ እንደሌለው አስታውቋል።

አሜሪካ ቲክቶክ እንዲሸጥ ወይም በአሜሪካ ውስጥ እንዲታገድ የሚያስገድድ ሕግ ማውጣቷን ተከትሎ የቲክ ቶክ እናት ካምፓኒ ቢዝነሱን የመሸጥ ፍላጎት እንደሌለው እየተናገረ ነው።

የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ቲክ ቶክ “ሕገ-መንግስታዊ አይደለም” ያለውን ይህንን ሕግ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ በመሄድ እንደሚቃወም ገልጿል።

ባይትዳንስ መግለጫውን ያወጣው “ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ” በተሰኘ ድረ-ገጽ ላይ ኩባንያው በአሜሪካ ውስጥ የቲክ ቶክ ኦፕሬሽን ከሚሰጠው ስልተ ቀመር (አልጎሪዝም) ውጭ ሊሸጥ የሚችለውን እየመረመረ ነበር የሚል መረጃ ከወጣ በኋላ ነው።

ኩባንያው ባይትዳንስ ቲክ ቶክን እንደሚሸጥ አድርገው የውጭ ሚዲያዎች የሚዘግቡት ከእውነት የራቀ፤ የውሸት ወሬ ነው ሲል ማጣጣሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

የሽያጭ ወይም የእገዳ እርምጃውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ረቡዕ እለት መፈረማቸው ይታወሳል።

ቻይና በግል ኩባንያዎች ላይ የምታደርገው ጥብቅ ቁጥጥር ተከትሎ በአሜሪካ እና በሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በባይትዳንስ ላይ ምን ያህል ቁጥጥር እንዳለው ለማወቅ አለመቻሉ ስጋት ፈጥሯል።

ቲክ ቶክ የቻይና መንግስት በባይትዳንስ ላይ ቁጥጥር አለኝ የሚለውን የይገባኛል ጥያቄ ደጋግሞ ውድቅ አድርጓል።

የቲክ ቶክ አለቃ ሹ ዚ ቼው በዚህ ሳምንት በዚሁ መድረክ ላይ በተለጠፈው ቪዲዮ ላይ “እርግጠኞች ነን እናም በፍርድ ቤት ለመብቶቻችሁ መታገላችንን እንቀጥላለን” ሲል ገልጿል።

“እውነት ከእኛ ጋር ነው፣ ሕገ መንግስቱ ከጎናችን ነው… እርግጠኛ ሁኑ የትም አንሄድም” በማለትም አክሏል።

በቲክ ቶክ መረጃ መሠረት የባይትዳንስ ካምፓኒ ቻይናዊ መስራቾች 20 በመቶ ብቻ የአክሲዮን ድርሻ አላቸው። 60 በመቶ ያህሉ በተቋማዊ ባለሀብቶች የተያዘ ሲሆን ዋና ዋና የአሜሪካ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ካርላይል ግሩፕ፣ ጄኔራል አትላንቲክ እና ሱስኩሃና ኢንተርናሽናል ግሩፕ ባለድርሻዎች ናቸው።

ቀሪው 20 በመቶ በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰራተኞች የተያዙ ሲሆን በባይትዳንስ ካምፓኒ ውስጥ አምስት የቦርድ አባላት አሜሪካዊያን ናቸው።

አዲሱ አሜሪካ ያጸደቀችው ሕግ እገዳው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ባይትዳንስ ቢዝነሱን ለመሸጥ ዘጠኝ ወራት እና ተጨማሪ የሶስት ወር የእፎይታ ጊዜን ይሰጠዋል።

ይህ ማለት የ2024 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው ስልጣን ከያዘ በኋላ የሽያጩ ቀነ ገደብ በፈረንጆቹ 2025 ይጠናቀቃል።