በትራንስፖርት ዘርፍ 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ የተሽከርካሪ ግዢ መቅረቡ ተገለጸ

 

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለማገዝ በ30 በመቶ ቅድመ ክፍያ የተሽከርካሪ ግዢ መቅረቡን ሔሎ መኪና አስታወቀ።

በትራንስፖርት ዘርፉ የሚታየውን የአቅርቦትና የግዢ ችግር ለመቅረፍ ሔሎ መኪና ከደቡብ ግሎባል ባንክ ጋር በመሆን ህብረተሰቡ በቀላሉ የመኪና ባለቤት የሚሆንበትን አማራጭ መፍጠሩን የድርጅቱ መሥራች አቶ ዳንኤል ዮሐንስ ገልጸዋል።

ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡት ተሽከርካሪዎች ያላገለገሉ አዳዲስና ዜሮ ዜሮ መኪናዎች መሆናቸውን ተናግረው ይህም መንግሥት የካርቦን ልቀትን ከመቀነስ አኳያ ያስቀመጠውን የአካባቢ ጥበቃ መርህ የተከተለ ነው ብለዋል።

ከደቡብ ግሎባል ባንክ ጋር በመሆን ተጠቃሚዎቹ በ30 በመቶ ቅድመ ክፍያ ከፍለው ቀሪውን 70 በመቶ ክፍያ በሰባት አመታት ውስጥ የሚከፍሉበት ስርዓት መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት።

የደቡብ ግሎባል ባንክ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ እንዳልሽ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፣ ጉዳዩ አገራዊ አስተዋጽኦ ያለው የስራ ዐሳብ በመሆኑ ባንኩ ተቀብሎት ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።

ከቢዝነስ አጋርነት ባለፈ ማህበራዊ ሃላፊነትን መወጣትና በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር የመቅረፍ አካል መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚህም የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት መሆን የሚፈልጉ የህብረተሰቡ ክፍሎች አስፈላጊ የሆኑ የዶክመንትና 30 በመቶ ቅድመ ክፍያውን ካሟሉ ብድሩን ያለ ምንም ውጣ ውረድ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ከግል ተጠቃሚነት ባለፈ በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አቅርቦቱ አጋዥ እንዲሆኑ በኮድ 3 እና ሁለት መዘጋጀታቸውም ተነግሯል። (ምንጭ ፡- ኢዜአ)