የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ዘርፍ 1.2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማስገኘት መታቀዱ ተገለጸ

የምግብ፣ የመጠጥ እና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዘርፍ በ10 ዓመታት መሪ ዕቅድ 1.2 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት መታቀዱ ተገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ የውጭ ንግዱን ለማበረታታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቷል።

ከኢንስቲትዩቱ ፍቃድ ወስደው የሚሰሩ 1 ሺ 390 በመጠጥ፣ ምግብ፣ አትክልትና የፍራፍሬ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በስኳር እና ጣፋጭ በቅባት እህሎች ማቀነባበር የተሰማሩ አምራች ድርጅቶች የሚገኙ ሲሆን፣ 65 የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብሏል።

ከዘርፉ በ2012 በጀት አመት 38.1 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም በአምስት ወራት ውስጥ 28.1 ሚሊየን ዶላር መገኘቱ ተገልጿል ።

በአስር አመታት መሪ ዕቅድ ሊገኝ የታቀደው የ1.2 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ አምራች እንዱስትሪውን በማበረታታት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ፣ በቀጣይ አመታት የኃይል መቆራረጥ በማስቀረት እና የስኳር ምርትን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በማሟላት እንዲሁም ትርፍ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ ለማግኘት የታሰበ እንደሆነ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ 80 በመቶ የመድኃኒት እና ፋርማሲዩቲካል ፍላጎቷን ከውጭ የምታስገባ በመሆኑ ይህንን ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና ለዘርፉ በቂሊንጦ ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ፖርክ መገንባቱ ተገልጿል።

(በምንይሉ ደስይበለው)