በትግራይ ክልል ሲካሄድ የቆየው የብቃት ምዝና አትሌቲክስ ውድድር ተጠናቀቀ

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ለአንድ ሳምንት ያህል ሲካሄድ የቆየው የብቃት ምዘና የአትሌቲክስ ውድድር ተጠናቋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አትሌትክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በነበረው ችግር ለ7 ወራት ያህል ተቋርጦ የቆየውን የአትሌቲክስ ውድድር ማስቀጠል ተችሏል።

በትግራይ ዓለም አቀፍ ስታድየም ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2013 ዓ.ም ሲካሄድ በቆየው ውድድር ከእንደርታ እና ህንጣሎ ዋጀራት ወረዳዎች እና መቐለ ከሚገኙ 5 ክፍለ ከተሞች የተመረጡ 261 አትሌቶች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

አትሌቶቹ በ100፣ 800፣ 1 ሺህ 500፣ 3 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ርቀት የብቃት ምዘና ውድድር አካሂደዋል ብለዋል። አሎሎ፣ ዲስክና ጦር ውርወራም የውድድሩ አካል እንደነበሩም ጠቅሰዋል።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች፣ ኮኮብ አሰልጣኞች፣ ተሳታፊ ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞች የገንዘብ፣ የዋንጫና የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በውድድሩ በ100 ሜትር 1ኛ በመውጣት የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነችው አትሌት ፋና አጽበሀ በሰጠችው አስተያየት፤ ስፖርት የተረበሸ አእምሮን የማከም ብቃት ያለው በመሆኑ ውድድሩ በመዘጋጀቱ ተደስቻለሁ ብላለች።

በሌላ በኩል ክልሉ በቶክዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን በመወከል የሚወዳደሩ 7 አትሌቶችን ማስመረጡን አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል።

ከተመረጡት አትሌቶች መካከል ለተሰንበት ግደይ እና ጽጌ ገብረሰማ በ10 ሺህ ሜትር እንዲሁም ጉዳፍ ጸጋይ በ5 ሺህ ሜትር፤ ከወንድ አትሌቶች ደግሞ በሪሁ አረጋዊና ሀጎስ ገብረህይወት በ10 ሺህ ሜትር እንደሚሳተፉ ጠቅሰዋል።