የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የምርጫውን ውጤት አስቀድመው ከማብሰር ሊቆጠቡ ይገባል-ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ

ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – ቦርዱ ውጤት ሳይገልጽ ከምርጫ ጣቢያ ውጤት በመነሳት “እከሌ አሸነፈ” የሚል መረጃ የሚለቁ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተከታይ ያላቸው አክቲቪስቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳስቧል።

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ በሰጠው መግለጫ  በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ መጠናቀቁንም ገልጿል።

የቦርዱ ኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ በመግለጫቸው ምርጫ በተጠናቀቀባቸው አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ ቆጠራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት የምርጫ ክልል ውጤት ይገለፃል፤ ወደ ዋናው ማዕከል ገብቶ በአስር ቀናት ውስጥም ጊዜያዊ ውጤት ይገለፃል ብለዋል።

በትናንትናው እለት ድምፅ መስጠት ባልተጠናቀቀባቸው የሲዳማና ጋምቤላ ክልል ምርጫ ክልሎች ቁሳቁስ ተሟልቶ ድምጽ እየተሰጠ በመሆኑ ዛሬ ይጠናቀቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።