በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመራጭ ተመራጭ ትስስር ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

መጋቢት 11/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመራጭ ተመራጭ ትስስር ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 63 ለንግድ ሥራ የሚሆኑ ሼዶችና 271 ለከተማ ግብርና የሚሆኑ መሥሪያ ቦታ ለወጣቶች አስረክበዋል፡፡
ከንቲባዋ መርሃ ግብሩ ላይ በኅልውና ትግሉ ላይ በጋራ ሰርተን ውጤት እንዳስመዘገበነው ሁሉ በሌሎች የልማት ሥራዎችም ድላችንን ለመድገምና የመረጠንን ሕዝብ ለመካስ እንዲቻል በጋራ እየተደጋገፍን እንዲሁም ከመረጠን ሕዝብ ጋር በጋራ እየተመካከርን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል።
በምርጫ ወቅት ከመረጣችሁን ቃላችንን ጠብቀን እናገለግላችሏለን ብለን ቃል ገብተን ነበር ያሉት ከንቲባዋ ይህንን ቃላችንን ምንጊዜም ቢሆን አናጥፈውም እናገለግላችኋለን ሲሉም አክለዋል፡፡
ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪውን ወክለው የተመረጡ የምክር ቤት አባላት ከመራጩ ሕዝብ ጋር የሚገናኙበት የሕዝብ ተመራጮች የትስስር አደረጃጀት መመሪያ ተግባራዊ መደረጉ ይታወቃል፡፡