መስከረም 15/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ባደረገው ወረራ 275 ሺሕ ሄክታር መሬት ሳይታረስ መቅረቱን እና በዘር የተሸፈነ አንድ ሚሊየን ሄክታር በእንክብካቤ እጦት ተበላሽቶ እንደቀረ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ አሸባሪው ሕወሓት ባካሄደው ወረራ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ ዋግህምራ እና ሰሜን ጐንደር ብቻ 275 ሺሕ ሄክታር መሬት ሳይታረስ መቅረቱን ገልጸዋል።
በእነዚህ አካባቢዎች አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ቢሆንም በአሸባሪ ቡድኑ የግፍ ወረራ ምክንያት እንክብካቤ ሳይደረግለት በእንስሳት እንዲበላ በመደረጉ የተዘራው ሰብል ተበላሽቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ሳኒ ገለጻ፣ አሸባሪ ቡድኑ በግብርናው ዘርፍ ያደረሰው የጉዳት መጠን ጠቅለል ያለ ጥናት እየተጠና ነው።
ሰላም በሆኑ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ቢሆን ሚሊሻውና ልዩ ኃይሎች በመዝመታቸው፣ ወላጆቻቸውን በግብርና እርሻ ያግዙ የነበሩ ወጣቶች አሸባሪውን የትህነግ ኃይል ለመመከት ግንባር በመሰለፋቸው ምክንያት የሚታጣው ምርት በባለሙያዎች እየተጠና ሲሆን፣ የማካካሻ ስራ ለመስራት የጋራ ንቅናቄ ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሚታጣውን ምርት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ተጨማሪ ምርት እንዲመረት በማድረግ የሚፈጠረውን ክፍተት የማካካስ ስራ ይሰራል ያሉት አቶ ሳኒ፣ በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ምክንያት የሚታጣውን ምርት ለመተካት በሚያስችል ደረጃ ለመስራት በእቅድ ላይ የተመሰረተ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል።