ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ”ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሊዊ ተራራ ላይ የጀመሩት፡፡
ሦስተኛው ሀገር አቀፍ ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የማልበስ ዘመቻ እንደበፊቱ ሁሉ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ በመርሃ ግበሩ ላይ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል የታቀደውን ስድስት ቢሊዮን ችግኝ ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድርሻቸውን ለመወጣት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በመርሃ ግብሩ ላይ መገኘታቸውን እና የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ በአረንጓዴ አሻራ ምድርን ማልበስ እንዳለ ሆኖ ሰዎች በብርድ እና ዝናብ ሲሰቃዩ ማየት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የመተከል ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በለሚደረገው ጥረት የ1 ሚሊዮን ብር የሚገመት የቤት ክዳን ቆርቆሮ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
እንደ አሚኮ ዘገባ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ አበበ (ዶክተር) የሳይንስና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እና የአማራ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረምና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ታፈረ መላኩ (ዶክተር) ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በመርሃ ግብሩ ተገኝተዋል፡፡