ሚኒስቴሩ የሂሳብና የሳይንስ ትምህርትን ለማሻሻል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒመም ለርኒንግ ኮምፒተንስ ኢትዮጵያ ከተባለ ጀሀገር በቀል ድርጅት ጋር በሂሳብና በሳይንስ ትምህርት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሟል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ገረመው ሁሉቃ (ዶ/ር) እና የሚኒመም ለርኒንግ ኮምፒተንስ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ደምሴ ናቸው የተፈራረሙት፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱ የሂሳብና የሳይንስ ትምህርት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጅነሪንግ እና ሂሳብ ትምህርቶችን ለማሻሻል ያስችላል ተብሏል።

የሂሳብና የሳይንስ ትምህርት ፈጠራዎችን በቴክኖሎጂ አሰራር በመደገፍ ለተማሪዎች ፍላጎትና ዝንባሌ አጽንኦት እንደሚሰጥ በስምምነቱ ተጠቅሷል።

የሂሳብና የሳይንስ ትምህርት ጤናማ አካባቢን በመፍጠር ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ምቹ የጥናትና የመማሪያ ቦታዎች መፍጠር እና የሂሳብና የሳይንስ ትምህርት መምህራን የማስተማር ክህሎት ማሳደግም የመግባቢያ ስምምነቱ አንዱ አካል ነው ተብሏል።

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።