በአማራ ክልል የወሰዱትን መሬት ማልማት ያልቻሉ የ116 ባለሃብቶች ውል ተቋረጠ

መጋቢት 13/2013 (ዋልታ) – በእርሻ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው በገቡት ውል መሰረት ማልማት ያልቻሉ የ116 ባለሃብቶችን ውል ማቋረጡን የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታወቀ።
ባለሃብቶቹ በገቡት ውል መሰረት የወሰዱትን መሬት በአግባቡ እንዲያለሙ ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩ ቢሆንም፣ በተደረገላቸው ድጋፍ ልክ እንዲያለሙ የተሰጣቸውን መሬት ሳያለሙ ጦም በማሳደር፣ ለሶስተኛ ወገን በማከራየትና ከ50 በመቶ በታች የልማት አፈፃፀም በማሳየታቸው እርምጃ መወሰዱን በቢሮው የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ባለፉት አራት ወራት በተወሰደው እርምጃም ውላቸውን በማቋረጥ በባለሃብቶቹ ተይዞ የነበረ ከ19 ሺህ 500 ሄክታር በላይ በማስመለስ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል።
መሬቱ ከባለሀብቶቹ የተመለሰው በምዕራብ ጎንደር፣ አዊ ብሄረሰብ አስተዳደር እና ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የወሰዱትን መሬት በአግባቡ ያላለሙ 126 ባለሃብቶች ላይ ደግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ጠቁመዋል።
ቢሮው ከባለሃብቶች ነጥቆ ወደ መሬት ባንክ ያገባውን ጨምሮ ከ21 ሺህ 500 ሄክታር በላይ የማልማት አቅም ላላቸው ባለሃብቶች በጨረታ አወዳድሮ ለማስተላለፍ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት የተረከቡትን መሬት በገቡት ውል መሰረት ያላለሙ 74 ባለሃብቶችን ውል በማቋረጥ ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለሌሎች አልሚ ባለሃብቶች መተላለፉን አስታውሰዋል።
ባለፈው ዓመት የእርሻ መሬት በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ በጨረታ አሸንፈው አንድ ሺህ ሄክታር ተረክበው ማልማት እንደጀመሩ የተናገሩት ደግሞ ባለሀብት የሆኑት አቶ ሙሏለም ሽፈራው ናቸው።
መሬቱን የተረከበቡት ሰኔ መጨረሻ ላይ መሆኑን አወስተው የእርሻ መሬት ደግሞ ሰፊ ጊዜና ዝግጅት የሚጠይቅ ስለነበር የተረከቡትን መሬት ከጅምር ባለፈ ማልማት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
በመጪው የመኽር ወቅት መሬቱን በቅባትና ሌላም ሰብል ለማልማት ሁለት ዶዘርና ሁለት ትራክተሮችን ከወዲሁ አስገብተው የምንጣሮና የእርሻ ስራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው ባለሀብት አቶ ሃብቴ ጥላሁን በበኩላቸው፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ አዲስ ዓለም ቀበሌ ባለፈው ዓመት ከተረከቡት 629 ሄክታር መሬት 180 ሄክታሩን በአኩሪ አተር፣ ማሽላ፣ ሰሊጥና ጤፍ ማልማታቸውን አስታውሰዋል።
በመጪው የመኽር ወቅትም በይዞታቸው በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል 191 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት በ488 ባለሃብቶች በተለያየ የሰብል ዓይነት እየለማ እንደሚገኝ ከገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።