በአሰላ ከተማ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከናወነ

ሰኔ 16/2013 (ዋልታ) – “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአሰላ ከተማ ተከናውኗል፡፡
መርሀግብሩ ችግኝን ከመትከል ባለፈ ሰላም እና አንድነት መትከል የሚል ዓላማን ያነገበ ነው ተብሏል።
መርሀ ግብሩ በምርጫ ማግስት መካሄዱም ኢትዮጵያውያን ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው ሲሉ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ ተናግረዋል።
ለዓለም የሚተርፍ የተስተካከለ የአየር ንብረት ለማኖር ችግኝ ተክለናል ያሉት ዶ/ር አለሙ ጥላቻን እየነቀልን ኢትዮጵያ ላይ አንድነትን፣ መተሳሰብን መትከል ይኖርብናል ነው ያሉት።
6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመገንባት በምታደርገው ጉዞ መልካም አሻራን ጥሎ አልፏል ለዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ ሚንስትር ዴኤታዎች፣ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ሀላፊ አክሊሉ ታደሰ፣ ከየክልሉ የተውጣጡ የብልፅግና ወጣቶች ሊግ አባላትን ጨምሮ አርቲስቶች እና ከየክልሉ የተውጣጡ ወጣቶች በመርሀግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
(በትዕግስት ዘላለም)