በመተከል ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች ወደ የአካባቢያቸው እየተመለሱ ነው

ሰኔ 16/2013(ዋልታ) – በመተከል ዞን በነበረው ግጭት ከማንዱራ ወረዳ ፎቶ ማንጃሪ ቀበሌ ተፈናቅለው የነበሩ 279 አባወራና እማወራዎች ወደ አካባቢያቸው ተመለሱ።

የአገር መካላከያ ሰራዊት ምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረኃይል ኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ፤ ወደየአካባቢያቸው ለተመለሱት ዜጎች የተዘጋጀላቸውን ጊዜያዊ ማቆያና መሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

በዞኑ ተከስቶ የነበረው ችግር እየተሻሻለ መጥቶ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው መመለሳቸው መልካም መሆኑን ገልጸው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ይሰራል ብለዋል።

በቀጣይ ኑሯቸውን በተረጋጋ ሁኔታ በመምራት ወደ እርሻና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲገቡ ለማስቻል የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት ደህንነታቸውን በመጠበቅ በቅርበትና በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የማንዱራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉኬ ግዡ፤ በአካባቢውን ጸጥታ ለማስፈን የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብርኃል ባከናወናቸው የተለያዩ ተግባራት ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።