በአሸባሪው ትሕነግ ለተጎዱ ወገኖች የኢትዮ ቴሌኮም ድጋፍ

መስከረም 15/2014 (ዋልታ) በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምሥራቅ ሪጅን በአሸባሪው ትሕነግ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ፡፡

በወረባቦ ወረዳ 09 ጎሀ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመገኘት በ15 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ ተማሪዎች 64 ሺሕ 428 ደብተሮችን አስረክቧል።

የትምህርት ቁሳቁሱን ለማሟላት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ምሥራቅ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ማስረሻ ገበየ ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ በመላው ኢትዮጵያ በ600 ትምህርት ቤቶች 600 ሺሕ ደብተሮችን በማዳረስ አገራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል።

የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ካሊድ ሙሐመድ ኢትዮ ቴሌኮም ለተማሪዎች ያደረገው ድጋፍ የተጎጅ ቤተሰቦችን ወጪ የሚቀንስ ነው ብለዋል፡፡ ስለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

በተያያዘ የኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ሰራተኞች ከ200 ሺሕ ብር በላይ ወጪ በማድረግ በሽብር ቡድኑ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን አሚኮ ዘግቧል።