ኅዳር 17/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ ‘ከተማዬን አፀዳለሁ፤ ፅዳትን ባህል አደርጋለሁ” በሚል ለቀጣይ 3 ወራት የሚቆይ የፅዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ ተካሄደ።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ የፅዳት ንቅናቄውን ባስጀመሩበት ወቅት ፅዳት የከተማው ባህል ሆኖ እንዲዘልቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
አብላጫው የከተማው ነዋሪ እያፀዳ ጥቂቶች ከተማውን እንዲያቆሽሹ መፍቀድ የለብንም ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ በየነ በቀጣይ የከተማውን ፅዳት በግድየለሽነት በሚያቆሽሹ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና ተቋማት ላይ ህግና ደንብን መሠረት ያደረገ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
ከተማዋ ፅዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን በማድረግ ረገድ በከተማ አስተዳዳሩ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራት በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በባለቤትነት ስሜት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የከተማው ፅዳትና ውበት መጠበቅ የሚጠቅመው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ አካባቢያቸውን የሚያቆሸሹ ጥቂት አካላት ህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ አስፈላጊው ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW