በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የፅዳት ዘመቻ መርኃግብር ተካሄደ

ኅዳር 12/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች “እኔ ለከተማዬ የሰላም ዘብ፤ ለፅዳቷ ደግሞ አምባሳደር ነኝ!” በሚል መሪ ቃል የፅዳት ዘመቻ መርኃግብር ተካሄደ።
በአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አስተባባሪነት የተወጠነው ሁሉን አቀፍ የፅዳት ንቅናቄ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከማለዳው 12:00 ጀምሮ ተካሂዷል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ንቅናቄ ላይ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የክፍለ ከተሞች አመራሮች፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የፅዳት ሰራተኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት ሕዳር 12ን ጠብቆ ደረቅ ቆሻሻን ሰብስቦ ማቃጠል ሀብትን የሚያወድም እና አካባቢን የሚበክል ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ፅዳት በዓመት አንድ ቀን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የሚከናወን የማያቋርጥ ሂደት ስለሆነ መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬተሪ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡