በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርኃ ግብር የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል

መጋቢት 27/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ “ኢፍጣራችን ለወገኖቻችን” በሚል መሪ ሀሳብ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርኃ ግብር የፊታችን ቅዳሜ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

የኢፍጣር ፕሮግራሙ ጊዜያዊ አስተባባሪ ፈይሰል ከማል መርኃ ግብሩን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ የጎዳና ላይ የኢፍጣር ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

የጎዳና ላይ ኢፍጣሩ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ከሃላል ፕሮሞሽንና ነጃሺ የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ታላቅ የኢፍጣር ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰው በመተባበር እና በመተጋገዝ የኢትዮጵያን እሴት በሚያጠናክር መልኩ የሚከናወን መርኃ ግብር መሆኑንም ተናግረዋል።

በዕለቱ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉና ችግር ለገጠማቸው ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰብ ስራም ይከናወናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በኢፍጣር መርኃ ግብሩ ላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል።

መርኃ ግብሩን ከ4 ሺሕ የሚበልጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እንደሚያስተባብሩትም ተጠቁሟል።