የእብድ ውሻ በሽታ እና ጥንቃቄዎቹ

 

ጤና ደጉ

የእብድ ውሻ በሽታ እና ጥንቃቄዎቹ

(በቴዎድሮስ ሳህለ)

በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ከ5 ሚሊዮን በላይ ውሾች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ350 ሺህ በላይ ውሾች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ብዙዎቹ ውሾች አይከተቡም፤ ባለቤትም የሌላቸዉ ቁጥራቸው የበዛ ነው፡፡

ውሾች ክትባት አለመከተባቸው ለማህበረሰብ ጤና እጅግ አስጊ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ያልተከተቡ ውሾች የእብድ ውሻ በሽታ (Rabies) ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ በሽታው ከውሾች ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በበሽታው በተያዘ ውሻ የተነከሰ ሰው ለህመሙ ይጋለጣል፤ የመዳን እድሉም አነስተኛ ነው፡፡

የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረስ የሚመጣ እና በልዩ ልዩ እንስሳት ንክሻ  ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው:: ይህ በሽታ በመላው ዓለም የሚገኝ ሲሆን ከ90%  በላይ በሽታው የያዛቸው ሰዎች  ለሞት እንደሚዳርግ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ህብረተሰቡ እብድ ውሻ በሽታ ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን ፣የበሽታው ክትባት መድሃኒት እጥረት በ በሽታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርለታል፡፡

 የእብድ ውሻ በሽታን እንዴት መከላከል  ይቻላል?

ውሻ በዚህ በሽታ እንዳይያዝ በቀላሉ ማድረግ የሚቻለው የቤት ውሾች በዚህ በሽታ እንዳይያዙ ክትባት በመስጠት ነው፡፡

በዚህ በሽታ ላይ ማህበረሰቡ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እና የእብድ ውሻ ንክሻን መከላከል ነው፤

እብድ ውሻ ሰውን እንዳይነክስ ያበደ ውሻ የሚያሳያቸውን ምልክቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ያበደ የቤት ውሻ ከሚያሳያቸው ምልክቶች በተለይም ወደ መጀመሪያ አካባቢ፣ ውሻው ከቀድሞ ሁኔታው በተለየ ሁኔታ እረፍት አጥቶ ወዲህ እና ወዲያ መንከላወስ፣ ቀደም ሲል የማይተናኮላቸውን ነገሮች ወይም ሰዎች እና እንስሳትን መተናኮል፣ መብራት ሲበራበት እና ድምጽ ሲሰማ መፍራት ናቸው፡፡

በሽታ በውሻው ላይ እየጠናበት በሚሄድበት ጊዜ

  • ጨለማ ቦታ ሄዶ መደበቅ፣
  • ምግብ ሲሰጠው መዋጥ አለመቻል፣
  • ምራቁን ማዝረክረክ/ ማንጠባጠብ፣
  • መድከም (አቅም ማጣት)፣
  • ቀደም ሲል የማይበላውን (የማይመገበውን) ነገሮች መብላት እና
  • ውሃን ሲያይ ወይም ሲረጭበት ፍርሃት ማሳየት

 ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ክትባት መስጠት ፡-

  • በበሽታው የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ ለሆኑ ሰዎች፣
  • በበሽታው ላይ ምርምር በሚደረግበት ላብራቶሪለሚሰሩ ሰዎች፣
  • በእንስሳት እንክብካቤ እና  ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሰዎች፣
  • በሽታው በብዛት ሊገኝበት በሚችልባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ህፃናት፣
  • በተለያዩ ምክንያቶች በሽታውን ከሚያስተላልፉ እንስሳት ጋር ረጅም ጊዜ አብሮ ለሚያሳልፉ ግለሰቦች ክትባቱን መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

በበሽታው የተለከፈ ሰው ሊያሳያቸው የሚችላቸው ምልክቶች፡-

በሽታው ያለበት ውሻ ሰውን ከነከሰ በኋላ የበሽታው ምልክት በሰው ላይ የሚታይበት የቆይታ ጊዜ  የተነከሰው የሰውነት ክፍሎችን መሰረት የሚያደርግ ነው:: ከአንጎል ርቆ የሚገኝ እንደ እግር ያለውን የሰውነት ክፍል የበሽታው ምልክቶች መታዬት የሚጀምሩት ዘግይቶ ነው፡፡

ወደ አንጎል ቀረብ ያለ የሰውነት ክፍል እንደ የራስ ቅል (Head) ከነከሰ ደግሞ ምልክቶቹ በቸጭር ጊዜ መታዬት ይጀምራ፡፡ ምክንያቱም ቫይረሱ በአጭር ጊዜ አንጎል ውስጥ መድረስ ስለሚችል፡፡

በበሽታው በተያዘ ውሻ የተነከሰ ሰው በአማካይ ከ2-3 ወራት ጊዜ ውስት ምልክት ሊያሳ ይችላል፡፡ ወደ አንገት በቀረበ ቦታ ላ የተነከሰ ሰው በአንድ ሳምንት ውስጥ ምልክቶቹ ሊታዩበት ይችላል፡፡

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ላይ የሚታይ ምልክቶች፡-

  • የሰውነት ትኩሳት መጨመር፣
  • የሰውነት መቃጠል እና ውጋት ስሜት በቁስሉ አካባቢ መሰማትን ያሳያል፡፡
  • ውሃ መፍራት፣
  • ከቤት ለመውጣት መፍራት
  • እና የመሳሰሉት ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ እነዚህን ምልክቶች ከታዩ በኋላ ይህ በሽታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህይወትን ይቀጥፋል፤ ይህ በሽታ አንድ ጊዜ ከያዘ በኋላ የሚደረገው ህክምናም ህይወትን ማትረፍ አይችልም፡፡

በበሽታው በተጠረጠረ ውሻ የተነከሰ ሰው ምን ማድረግ አለበት?

  • የተነከሰው ቦታ ወዲያውኑ ጊዜ ሳይሰጥበት በትክክል በንጹህ ውሃ እና በሳሙና ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ማጠብ ግዴታ ነው::
  • በፍጥነት አቅራቢያ ወዳለ የጤና ተቋም በመሄድ ክትባት መውሰድ ይገባል::

ክትባቱ እንደ ዱሮው ጊዜ ለ14 ቀናት የሚሰጥ ሳይሆን ለ5 ቀናት የሚሰጥ አወሳሰዱም በጣም ቀላል የሆነ ነው፡፡ ይህ ክትባት የሚሰጥበት 5 ቀናትም በመጀመሪያው ቀን፣ በ3ኛ ቀን፣ በ7ኛ ቀን፣ በ14ኛ ቀን እና በ28ኛ ቀን ላይ ነው፡፡

የጤና ባለሙያ ባዘዘው መሰረት (Immunoglobulin )የሚባል ተጨማሪ መድሃኒትንም መውሰድም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ያበደ ውሻ  በዋናነት ወደ ሰው ያስተላልፈው  እንጂ  በቫይረሱ የተያዘው ድመት፣ ከብት፣ ፍየል፣ ቀበሮ፣ ጥንቸል፣ የሌሊት ወፍ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ እና የመሳሰሉት የቤት እና የዱር እንስሳት ሰውን ነክሰው ምራቃቸውን ወይም ደማቸውን ወደ ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡