ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) በምንዛሬ እጥረት፣ በፀጥታ ችግር፣ በመሰረተ ልማት እጥረት እንዲሁም በግብዓት ችግር ምክንያት ከገበያ ውጪ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መመለሳቸውን አስታወቁ።
በኮሮና ቫይረስ እንዲሁም በሀገሪቱ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከምርት ውጪ ሆነው የቆዩ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየተመለሱ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በሰንዳፋ የሚገኘው የአፍራን ግሎባል ቢዝነስ የጁስ ማምረቻ ኢንዱስትሪ በምንዛሬ እጥረት ምክንያት ለ9 ወራት ከምርት ውጪ ሆኖ እንደነበር እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ሥራ መግባቱንና ምርት ማምረት መጀመሩን አስታውቋል።
በሱሉልታ የሚገኙ ሊትል አዲስ ኸልዝ ፉድ ካምፖኒ፣ በላያ ኢንዱስትሪያል የውሃ ማምረቻ ኩባንያ እንዲሁም ኤሌልቱ ወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በተደረገላቸው ድጋፍ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ግርማ ረጋሳ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከ130 በላይ ከገበያ ውጪ የሆኑ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ገልጸው ኢንዱስትሪዎቹ ያጋጠማቸውን ችግር በመፍታት ወደ ሥራ እንዲመለሱ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በመሰረተ ልማት ችግር እንዲሁም ከመሬት ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ኃላፊው ከምርት ውጪ የሆኑ ሁሉም ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
መንግሥት ለኢንዱስትሪዎቹ የሰጠው ትኩረት መልካም የሚባል ቢሆንም አሁንም ግን ሰፊ ሥራ መሰራት እንደሚገባው ኢንዱስትሪዎቹ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ምርት ማምረት ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል።
በዙፋን አምባቸው
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!