ምክር ቤቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር ዕይታ መራ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አይቶ ለዝርዝር ዕይታ መራ።

ምክር ቤቱ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራት ላይ ተወያይቷል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ባቀረቡት መግለጫ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የተቀመጠውን የሪፎርም አቅጣጫ ለማሳካት ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸው ተቋሙ ተልዕኮውን በብቃት መወጣት እንዲችል የአዋጅ ማሻሻያ መቅረቡን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ላይ የሚፈጸመውን ጦርነት የመመከት ሂደት በአግባቡ ካልተመራ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅምን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል በመሆኑ የሚቃጣውን የሥነ ልቦና ጦርነትን ለመመከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ተግባራትን በበላይነት የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም እንዲሆን በማስፈለጉ እነዚህን ተግባራት የሚያመላክት ድንጋጌ እንዲካተት ተደርጓ ብለዋል፡፡

እንደኢዜአ ዘገባ የምክር ቤቱ አባላት በረቂቁ ላይ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ለዝርዝር እይታ ረቂቅ አዋጅ 7/2014 ሆኖ በዋናነት ለህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW