በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን የመረጃ፣ ቢዝነስና መሰረተ ልማት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ተፈረሙ

ሐምሌ 21/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለውን የመረጃ፣ የቢዝነስና የመሰረተ ልማት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች ተፈረሙ።

ስምምነቶቹ በሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ በሚገኘው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባላት ነው የተፈረሙት።

በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ዓለም አቀፍ የመረጃ ደህንነትን በተመለከተ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈራረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ናቸው።

ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመረጃ ደህንነት ዘርፍ ላይ አቅምን ለመገንባት፤ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ እንዲሁም የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ አቅምን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል።

የሁለቱን አገራት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለማሳደግ ያለመው ስምምነት አንዱ ሲሆን ስምምነቱን የፈረሙት የሩሲያ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ኢጎር ቻሊክ ሩሲያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እና በሩሲያ የጉምሩክ አገልግሎት ኃላፊ ሩስላን ዳቪዶፍ መካከል የተፈረመው ሌላው ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል በዘርፉ ያለውን የክፍያና አገልግሎት ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል እንደሚሆንም ተነግሯል።

በተጨማሪም ስምምነቱ የኢትዮጵያና የሩሲያን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላልም መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡