መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ እና በጃፓን መንግስታት መካከል ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያና ለማዳበሪያ ግዢ የሚውል የ25 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ተፈረመ፡፡
ከፋይናንስ ድጋፉ ውስጥ 19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ትንንሽ ከተሞች ለመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ሲሆን 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ 2 ሺሕ 500 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ለመፈጸም የሚውል መሆኑ ታውቋል፡፡
በመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በትንንሽና በገጠር ከተሞች የሚኖሩ ከ47 ሺሕ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን የአፈር ማዳበሪያ ድጋፉም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የአፈር ማዳበሪያ የዋጋ ንረት በመጠኑ ለማረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ታምኖበታል ተብሏል፡፡
የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ መፈራረማቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡