የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

አንቶኒ ብሊንከን

መጋቢት 1/2015 (ዋልታ) የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሆነ ተገለጸ።

ሚኒስትሩ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ እና ኒጀር የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን በኢትዮጵያ የፊታችን ረቡዕ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሠላም ለማስፈን በተወሰዱ እርምጃዎች እና የጦርነት ማቆም ስምምነቱን ተከትሎ አፈፃፀሙ ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አጋሮችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ አካላትን በማነጋገር የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት፣ በምግብ ዋስትና እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ ይወያያሉ ነው የተባለው።

ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ አመላክቷል።