በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የሚያስችል ምክክር እየተካሄደ ነው

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) ኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን ለማስፋፋትና ጥቅም ላይ ለማዋል በሰነቃቸው ተልዕኮዎች ላይ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በመድረኩ ኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፉን ደረጃ ለማሳደግና ከፍ ለማድረግ ትልቅ ተግዳሮት እንዳለባት ጠቁመዋል።
በ2030 ሁሉንም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ቀርጻ እየተገበረች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ አባል በመሆኗ በጥምረቱ በሚሠሩ ፕሮግራሞች ዙሪያ ፍላጎቷን እንደገለጸች ጠቁመው የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ረገድ ጥምረቱና ሌሎች የልማት አጋሮች ለሚያደርጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ሶላር አልያንስ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመስኖ ለሚካሄድ ግብርና፣ በሐይቆች ወይም በግድቦች የውሃ አካላት ላይ ሊንሳፈፉ፣ በሕንጻዎች ጣሪያ ላይ ሊቀመጡ የሚችሉ የሶላር ፓኔሎችን በማድረግ ኢነርጂ ለማመንጨትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚሠራ ጥምረት ነው፡፡
በዚህም ዘላቂ የልማት ግቦች ግብ 7 እና 13 እውን ለማድረግ ሰፊ የፀሐይ ብርሃን ሀብት ባላቸው 102 አገራት ውስጥ የሚሠራ የአገራት ጥምረት መሆኑን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡