በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሂደትን የተመለከተ ሀገራዊ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – “የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የምክክር መድረክ በይፋ ተጀምሯል።

የምክክር መድረኩ በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለተከታታይ 4 ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባለፉት ሶስት ዓመታት መዋቅራዊ ችግሮች ናቸው የተባሉ ጉዳዮችን በጥናት የመለየት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በሂደቱም አንዳንዶቹ በረጅም ጊዜ የሚፈቱ እንደሆኑና የተቀሩትም በአጭር ጊዜ የሚፈቱ መሆናቸውን ተገንዝበናል ያሉት ሚኒስትሯ፣ የሚካሄደው ሀገራዊ ውይይት ለዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ወቅት መንግስት ያከናወናቸው ተግባራትና የመንግስት ተቋማዊ አደረጃጀቶች አቅም በሽግግር ወቅት የገጠሙ እድሎችና ችግሮችን ለመመልከት ያስችላል ብለዋል።

መድረኩ 4 የውይይት ሀሳቦች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በተለይም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር ሂደት፤ ብሔራዊ መግባባት፤ ምርጫ 2013 እና ከዚያ ባሻገር ያሉ ጉዳዮች የሚያስዳስሱ ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ለአራት ቀናት በሚዘልቀው ሀገራዊ የውይይት መድረክ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች በተሳታፊዎች ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋልም ነው የተባለው።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የፌደራልና ክልል መንግስታት የስራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ምሁራን፤ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

(በደረሰ አማረ)