በኦሮሚያ ክልል ከ11 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸው ተገለጸ

ግንቦት 24/2013 (ዋልታ) – በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ11 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።

የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በ2013 ዓ.ም በክልሉ የተተገበሩ የልማት ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ ያሉ የልማት እድሎችን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም በተወሰዱ እርምጃዎች በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በዋናነት ባለፈው አመት 6 ሺህ 4 መቶ ፕሮጀክቶች ተሰርተው ለአገልግሎት ይፋ መደረጋቸውን አስታውሰው፣ የተለያዩ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በዘንድሮው አመት 11 ሺህ 1 ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የመንገድ ልማት ዝርጋታ፣ መስኖ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የውሃ እና ሌሎች የህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶችንም ያካተቱ መሆናቸው ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ወደ 31 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ጭምር በአጠቃላይ ወደ አንድ ሚሊየን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩንም አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።

(በደረሰ አማረ)