ባንግላዴሽ ከህንድ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች

ግንቦት 24/2013(ዋልታ) – ደቡባዊ ኤስያ አገር ባንግላዴሽ  ስምንት ተጨማሪ በህንድ የተከሰተው  አይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ማግኘቷን ተከትሎ ከህንድ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷን የሃገሪቷ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡

ይህ አዲስ ዝርያ የሆነው ኮሮና ቫይረስ የተገኘው በሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ከዋና ከተማዋ ደህካ 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ  ሲሆን  እስካሁን ድረስም  በዚሁ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 31 ደርሷል ተብሏል፡፡

የበሽታው መከሰትን ተከትሎ ባንግላዴሽ ከህንድ ጋር የምትዋሰንበትን የድንበር አካባቢ ዝግ ማድረጓን አናዶሉ ዘግቧል፡፡

በሁለቱ ደቡብ ኤስያ ጎረቤት ሃገራት መካከል ሸቀጣ ሸቀጦችን ከሚያጓጉዙ ካርጎዎች በስተቀር በመሬት ላይ የሚደረግ የትኛውም አይነት ጉዞ ታግዷል፡፡

በዚህም በአካባቢው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሃገር አቀፍ ደረጃ እስከ ሰኔ 6 /2021 ድረስ የእንቅስቃሴ ገደቡ መራዘሙን በመረጃው ተመላክቷል፡፡

የሃገሪቱ የበሽታ መከላከል፣ ቁጥጥር እና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ኦፊሰር ዶ/ር ኤ.ኤስ.ኤም አላምጊር ከአናዶሉ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የጤና መመሪያዎችን በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ቀደም ሲል በባንግላዴሽ እና ህንድ መካከል በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ጥብቅ ገደቦችን መጣሉን ያስታወሱት ኦፊሰሩ ይህም ጥሩ ጅምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኦፊሰሩ አክለውም በአካባቢው የሚደረጉ መደበኛ ያልሆነ የሰዎች እንቅስቃሴ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የባንግላዲሽ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዛሂድ ማሌክ በትላንትናው እለት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት መንግስት በቅርቡ ህንድን በሚያዋስኑ ወረዳዎች ውስጥ ከባድ የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል እቅድ ተይዟል፡፡

አዲሱ የቫይረስ ዝርያ ይበልጥ እንዳይዛመት ሁሉም አካላት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በባንግላዲሽ  እስካሁን ድረስ በጠቅላላው በሃገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 619 ሲሆን 800 ሺህ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡